በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤና ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ሀገራዊ ንቅናቄ እንደሚከናወን ተገልፀ፡፡
ጥር 29/2013 ዓ.ም
ባህር-ዳር
***********************®*************************
ሀገር አቀፍ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ እና የተጠሪ ተቋማት የ2013 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግማገማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በግምገማ መድረኩ ላይ ለኮሚሽኑ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት፤የተለያዩ ባለድርሻዎች፤ የዘርፍ አረንጓዴ ልማት ተግባሪ ሚኒስትር መ/ቤቶች፤ የዘርፉ ክልል መ/ቤቶችና የልማት አጋር አካት የተሳተፉ ሲሆን ውይይቱም ከጥር 29 እስከ የካቲት 3/2013 ዓ.ም ቀጥሎ ይከናወናል፡፡
በውይይቱ በዘርፍ ደረጃ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራት ቀርበው በጥልቀት የሚገመገሙ ሲሆን የምክክር መድረኩን ተከትሉ በሁለት የተመረጡ ቦታቦች የመስክ ምልከታዎች በማካሄድ የተመዘገቡ መልካም ተሞክሮዎችን ምልከታና ልምድ ልውውጥ ይከናወናል፡፡
የምክክር መድረኩ የተካሄደበት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አካባቢ፣ ድንና ዱር እንስሳት ባለስልጣን ሀላፊ ዶ/ር በላይነህ አየለ ለታዳሚዎች የእንኳን መጣችሁ ንግግር በማድረግ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸውን አንኳር አንኳር ተግባራት ገልፀዋል፡፡ ሀላፊው በተጨማሪም ተሳታፊዎች በውቢቱ ባህር ዳር በሚኖራቸው ቆይታ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙና የክልሉን የተፈጥሮ ሀብቶች በሄዱበት ቦታ ሁሉ እንዲያስተዋውቁ ጥሪ አቅርበው የዕለቱ የክብር ዕንግዳና የግምገማ መድረኩን በንግግር የከፈቱትትን የአካባቢ፣ የደንና የዐየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር ፕሮፌሰር ፊቃዱ በየነ ጋብዘዋል፡፡
ክቡር ኮሚሽነሩ በመክፈቻ ንግራቸው እንደገለፁት "አሁን የምንገኝበት የዝግጅት ምዕራፍ የ10 ዓመታት የልማት ዕቅድ ተዘጋጅቶና በየደረጃው ለሚገኙ ተግባሪ አካላት ወርዶ ወደ ትግበራ የተገባበት የመጀመሪያው የስራ አፈፃፀም ዓመት መሆኑን ገልፀዋል፡፡"
ክቡር ኮሚሽነሩ አክለው እንደገለፁት "የኮሚሽኑ የአስር ዓመታት የልማት ዕቅድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተቀረፀው መሪ የልማት ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ የተዘጋጀ ሲሆን በዚህም ዕቅድ ከተለዩ አስር አበይት የልማት ምሰሶዎች (Development Pillars) ውስጥ አንዱ-ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስልት" መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በኮሚሽነሩ ንግግር ሌላው በዝርዝር የተብራራው ጉዳይ የዘርፉ የአስር ዓመታት የልማት ዕቅድ ዋና ዓላማ "ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ዕውን ለማድረግ የሀገራችንን የአካባቢ፣ የደን፣ የዱር እንስሳት እና ሌሎች የብዝሃ-ሕይወት ሀብትን በማልማት፣ በማንበር፣ በመጠበቅ እና ዘላቂ አጠቃቀምን በማስፈን ከአገር በቀል ኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ ጋር በማጣጣም፣ ጤናማ የስርዓተ ምህዳር መስተጋብርን በማሳደግ ዘላቂ አገራዊ ልማትና እድገት እንዲረጋገጥ ማድረግ መሆኑን ነው፡፡
በመድረኩ ላይ በጉልህ ከተነሱ አበይት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት ተጀምሮ ምልዐተ ህዝቡን ያንቀሳቀሰው "የአረንጓዴ አሻራ" መርሀ ግብር በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተግዳሮት ቢደቀንበትም በቁርጠኛነት መከናወኑ ተገልፆ ይህም አመርቂ ውጤት ህዝብና መንግስት ተባብረው ከሰሩ በአዳጋች ሁኔታ ውስጥም ጭምር ተአምር ማምጣት የሚያስችል ውጤት ማስመዝገብ የሚቻል መሆኑን ትምህርት የተገኘበት ሀገራዊ ንቅናቄ ሆኖ አልፏል ተብሏል፡፡ በመሆኑም ይህንን ህዝባዊ ንቅናቄ ግለቱን ጠብቆ በመቀጠል በቀጣይ ዓመታት ለማሳካት ኮሚሽኑ ያቀዳቸውን የችግኝ ተከላና ሌሎች የዘርፉ ዕቅዶችን ለማሳካት ሀገራዊ የህዝብ ተሳትፎና ንቅናቄ ለማከናወን በዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም በውይይት ሂደቱ ሁሉም አካላት በንቃት በመሳተፍና ለቀጣይ ስራቸው ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ለተግባራዊ ተልዕኮ እንዲዘጋጁ ጥሪ ቀርቧል፡፡