የአዲስ አበባ ከተማ እየተከሰተ ያለው የአየር ብክለት መጨመር በነዋሪዎች ጤና ላይ የመተንፈሻ አካላትና የልብ ህመም ችግር ሊያስከትል የሚችልና በዚህም ነዋሪዎች ለችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ይህን ችግር ለመከላከል በከተማ አስተዳደሩ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ከUSEPA እና ከUNEP ጋር በመተባበር ለከተማዋ የአየር ጥራት ማኔጅመንት ዕቅድ (Air Quality Management Plan) የማዘጋጀት ፕሮጀክት ተነድፎ በመተግበራ ላይ ይገኛል፡፡
በዚሁ ፕሮጀክት በከተማዋ በተመረጡ ቦታዎች ላይ የአየር ብክለትን ያለማቋረጥ የሚለኩ መሳሪያዎች ተከላ በዚህ ወር ተጀምሯል፡፡ ኮሚሽኑ በሚገኝበት ግቢ አንድ የተተከለ ሲሆን በቀጣይ ቀናት በሜክሲኮ፣ በመርካቶ፣ በረጲ (ቆሼ) እና በአራት ኪሎ የሚተከል ሲሆን በተጨማሪም በቃሊቲና ዊንጌት አካባቢ ለመትከል ታቅዷል፡፡
መሳሪያዎቹ የተለያዩ ብክለት ዓይነቶችን (O3, NOx, PM2.5, PM10, Temp) በየ10 ደቂቃ የሚለካ ሲሆን ውጤቱም በኦንላይን ቀጥታ እንዲታይ ይደረጋል፡፡ የልኬቱ ውጤት በከተማዋ እየደረሰ ያለውን የብክለት ደረጃ ለማወቅ፣ ከደረጃ ጋር ለማነጻጸር፣ የትኞቹ አካባቢ ላይ ችግሩ እንደሚጎላ ለማሳየት፣ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ እና ለጥናትና ምርምር ሥራ ያገለግላል፡፡
ምንጭ፡- አዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ኮሚሽን፡፡