በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምስራቅ ጎጃም ዞን በጮቄ ተራራ እና የተፋሰሱ ወረዳዎች ዙሪያ በተሰሩ የአካባቢ እንክብካቤና ስነ-ምህዳር ጥበቃ ስራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱ ተገለጸ ፡፡
መቀመጫውን በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ያደረገውና የብዝሀ-ሕይወት ጉዳዮች ለአየር ንብረት ለውጥ በማይበገር የልማት ስልት ውስጥ ተካቶ እንዲተገበር በሚሰራው ስትራተጂካዊ እርምጃ (Strategic Iniciative) ከደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ፣ ከዞኑ የገጠር መሬት አስተዳደር ጋር እና ከአካባቢው ህብረተሰብ ከተውጣጡ አካላት ጋር በመሆን ውይይት አካሄዱ፡፡ የውይይቱ ዓላማ ቀደም ብሎ በጥብቅ የስነ ምህዳር ሀብትነት የተከለለው የጮቄና ተፋሰሱን ነባራዊ ሁኔታ፣ እያገጋጠሙ ያለሉ ተግዳሮቶች ስለሚፈቱበት ሁኔተታ ለመምከርና የብዝሀ ህይወት ሳይቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሊያበረክት ስለሚገባው ጠቀሜታ ለምከር ነው፡፡
የብዝሀ-ሕይወት መካተቻና ማትጊያ ፕሮጀክት ከደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ እና ከዞኑ የገጠር መሬት አስተዳደር ጋር ህብረተሰቡን በማሳተፍ በጥምረት የሰሩትን ጥብቅ ስፍራ የማካለል ስራ እና በሂደቱ የተሰሩ ዝርዝር ስራዎችን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አብደታ ደበላ በውይይቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ የስነ ምህዳር ሀብቱ ለማህበረሰቡ በቀጣይነት ማበርከት የሚኖርበትን ፋይዳ ለመለየት የጮቄ ተራራ ስነ-ምህዳራዊ ሀብት በምን ደረጃ ላይ እንዳላ መለየት፤ ምን ምን እምቅ ሀብት እንዳለው ማስጠናት፤ አጠቃላይ ቆዳ ስፋቱን ከልሎ ዘመናዊ ካርታ ማዘጋጀት፤ ስለ እንክብካቤው ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት እና የመሬት አጠቃቀም ህገ-ደንብ ማዘጋጀት የሚሉት ጉዳዮች በዋናነት የተሰሩ ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም ከጥብቅ ስፍራው ክለላ ጎን ለጎን ማህበረሰቡ አማራጭ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችሉ የገቢ ምንጮች ላይ ማለተትም በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ ሀይል ቆጣቢ ምድጃዎችን በማሰራጨት እንዲሁም የስነ-ምህዳር ግልጋሎት ክፍያ ማህበረሰቡ እንዲያገኝ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሲሰሩ መቆየታቸውን እና ተስፋ ሰጪ ውጤት ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ አስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጮቄ ተራራ እና የተፋሰስ ወረዳዎች የተሰሩ የስነ-ምህዳር እንክብካቤ ስራዎችን በተመለከተ የአካባቢውን ማህበረሰብ እና የሀገር ሽማግሌዎችን ባወያዩበት ወቅት ተወያዮች ስነ ምህዳሩ መካለሉን እንደማይቃወሙ የጥበቃ እና እንክብካቤ ስራው ከተጀመረ አዳዲስ አዎንታዊ ለውጦችን እንዳዩ ገልፀዋል፡፡ ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው አክለው እንደገለፁት ስፍራውን የማካለሉና የመተዳደሪያ ህገ ደንብ የማዘጋጀት ሂደቱ በሚፈለገው ደረጃ የአካባቢውን ነዋሪዎች ጥቅም እንደሚያረጋግጥ በቂ ውይይትና ግንዛቤ ያልተጨበጠበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተነሱ ዝርዝር ሀሳቦችና ቀጣይ ስራዎች ላይ ከክቡር ፕሬዝዳንቱ ጋር በተደረገ ሰፊ ውይይት የአካባቢው ማህበረሰብ እና የአገር ሽማግሌዎች የተጀመረውን የማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራ እንክብካቤ የነዋሪዎችን ጥቅም ባስከበረ መልኩ ከአካባቢው ሙያተኞች ጋር እንደሚተገብሩ ስምምነት ላይ መድረስ ችለዋል ፡፡
ለበርካታ ወንዞች እና ምንጮች መፍለቂያ የሆነውን የጮቄ ተራራ እና የተፋሰስ አካባቢዎች ዘመናዊ በሆነ መንገድ በመንከባከብ እየታየ ያለውን ፍሬያማ ውጤት በትጋት በማስቀጠል ከጉዳት ለመታደግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ፡፡
የካቲት/2011 ዓ.ም፣ ደብረማርቆስ
***********///**********
በ: መዝገበ ታገሰ
-------