የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን “ብክለት ይብቃ-ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ ንቅናቄ አስጀመረ።
መጋቢት 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን “ብክለት ይብቃ-ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ ንቅናቄ አስጀመረ።
በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን ኢትዮጵያ ብክለትን ከመከላከል ረገድ የአረንጓዴ አሻራ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ ብክለትን በመቀነስ ምርታማነትን መጨመር እና ከተሞችን ከአካባቢ ብክለት በነፃ ሁኔታ ማልማት ላይ ትኩረት በመስጠት እየሰራች እንደምትገኝ ጠቁመዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለፃቸው በሀገር አቀፍ የስድስት ወራት ንቅናቄው ላይ “ብክለት ይብቃ-ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረውን ንቅናቄ መንግስት ትኩረት እንደሚሰጠው ገልፀው አካባቢን ከብክለት የተፈጥሮ ሀብትን ከብክነት መጠበቅ የመኖርና ያለመኖር ህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት መላው ህዝባችን ለንቅናቄው መሳካት ተሳታፊ እንዲሆን አቅጣጫ በመስጠት ንቅናቄው መጀመሩን አብስረዋል።
በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ የክልል ፕሬዝዳንቶች፣ ሚኒስትሮች፣ አጋር ድርጅቶች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።
ንቅናቄው ከመጪው ሚያዝያ እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም ለተከታታይ ስድስት ወራት የሚካሄድ እና በፕላስቲክ፣ የአየር፣ የዉሃ፣ የአፈር እና የድምፅ ብክለት ላይ ትኩረቱን በማድረግ ዛላቂ የአካባቢና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን