ብሄራዊ የተቀናጀ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ፖሊሲ በሀገራችን ያለመኖር ለልማት ስራዎች መፋጠን ማነቆ ከመሆን አልፎ ውሱን የሆነውን ሀብት ለወረራና ሽኩቻ ያጋለጠ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የተዘጋጀውን የምክክር መድረክ በንግግር የከፈቱት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ክቡር ፕ/ር ፈቃዱ በየነ እንዳሉት መሬት የክልሎች ሀብት መሆኑን ገልፀው በሀገር ደረጃ ብሄራዊ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ፖሊሲ በፌደራል መንግስት ሳይዘጋጅ መቆየቱ ለበርካታ የልማት ስራዎቻችን ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ገልፀው አሁን ባለንበት ደረጃ ብሄራዊ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ፖሊሲ በአስቸኳይ ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ መንግስት ቁርጠኛ አቋም መያዙን ገልፀዋል፡፡
ብሄራዊ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ፕሮጀክት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ገ/ትንሣኤ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንደገለፁት ብሄራዊ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ፖሊሲውን ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት በርካታ ጊዜ ተወስዶና ተሞክሮዎችም ታይተው የተዘጋጀ ሲሆን አሁን ፖሊሲው በሚገኝበት የማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ የጉዳዩ ቁልፍ ባለድርሻ የሆኑ አካላት የሚሠጡት ግብዐትም ስራውን አጠቃሎ ወደተግባር ለማስገባት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተለያዩና ጉዳዩ በይበልጥና በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ማለትም የከተማ አስተዳደሮች፣ የክልሎች መሬት አስተዳደር ቢሮዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የማህበረሰብ አካላት ተካፍለውበታል፡፡
በመክፈቻ ንግግራቸው ማሣረጊያ ክቡር ኮሚሽነሩ እንደገለፁት ጥናቱ አሁን ባለበት ደረጃ ወደትግበራ ሊያስገባ በሚያስችል ደረጃ ላይ መሆኑን ገልፀው በጥናት ሂደቱ ለተሳተፉ ባለሞያዎችና ጥናቱን ለደገፉት የጀርመን ተራድኦ ድርጅት፣ ዮ.ኤስ.አይ.ዲ እና ለአለም ባንክ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የካቲት 11/2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል፡፡
******************///*******************