የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ህጎችና አፈፃፀማቸውን አስመልክቶ ለሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለሞያዎች ስልጠና ሰጠ፡፡ ዛሬ በቡሾፍቱ ሮዝመሪ ሆቴል የተጀመረው ስልጠና ነገም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን የስልጠናው ዓላማም በአጠቃላይ አካባቢ፣ ደንና አየር ንብረትን የሚመለከቱ በተለይም ደግሞ የአካባቢ ብክለትና የደረቅና ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን አስመልክቶ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሞያዎችን አቅም በማጎልበት በጉዳዩ ላይ በቀጣይነት ማህበረሰባችንን የሚጠቅሙ ወቅታዊና ተከታታይ የሆኑ መረጃዎችን እንዲያደርሱ ለማስቻል ነው፡፡
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር ፕ/ር ፍቃዱ በየነ እንደገለፁት "ሀገራችን የቀየሰችው የአረንጓዴ ልማት ስልት በመሠረቱ የአካባቢ ጥበቃ፣ ደህንነትና ዘላቂ ልማትን ያማከለ በመሆኑ በርካታ የቴክኒክና የሀብት ድጋፍ አስገኝቶልናል፡፡ ይሁንና አሉ ኮሚሽነሩ አክለው የልማት ፖሊሲዎቻችን፣ ስትራቴጂዎቻችንና የነሱ ማስፈፀሚያ የሆኑት የአካባቢ ህጎቻችን ከሚደነግጉት ውጪ በአጠቃላይ በርካታ የአካባቢ መበከሎች በስፋት እየተከሰቱ ነው፡፡ በተለይም አሉ ኮሚሽነር የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች አያያዝና አወጋገድ ስርዐታችን በጊዜ መላ ካልተበጀለት ከፍተኛ የአካባቢና ማህበረሰብ ደህንነት ስጋትን የሚደቅንበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ብለዋል፡፡
ክቡር ፕ/ር ፍቃዱ በንግግራቸው ማሳረጊያ "የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና በሂደትም ለማቆም በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲፈፀም የሚጀመረውን ሀገራቀፍ ንቅናቄ አንድም እንደ ጥቃቱ ሰለባ ዜጋ አንድም ደግሞ ሙያዊ ስነ ምግባራችሁ በሚጥልባችሁ ሀላፊነት ሲባል በስራዎቻችሁ ውስጥ አካታሁ ለማህበረሰቡ ተከታታይ፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን እንድታደርሱ ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ" ብለዋል፡፡
በዛሬው የስልጠና ውሎ ባለሞያዎቹን ለቀጣይ ስራዎች ያነሳሳሉ ተብሎ የታመነባቸው በርካታ የህግና የጥናት ሰነዶች ማለትም፡-
- የኮሚሽን መ/ቤቱ አጠቃላይ መግለጫ፣
- የአካባቢ ህጎች አመሠራረትና እድገት፣
- በኢትዮጵያ ከብክለት መከላከል ጋር ተያይዞ የወጡ ፖሊሲዎች/ህጎች፣
- በሀገራችን የተሞች ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች አያያዝ፣አወጋገድ ስርዐት እድሎችና ተግዳሮቶችና
- ሀገራቀፍ የንቅናቄ ስትራተጂ ሰነዶች ቀርበዋል፡፡
በቀረቡዠት ሶስቱ ሰነዶች ላይም በአካባቢ ዘርፍ ም/ኮሚሽነር ክብርት ወ/ሮ ፍሬነሽ የተመራ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ ክብርት ም/ኮሚሽነሯ በእለቱ ውይይት ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት ለውይይት የቀረቡት ሰነዶች ተሳታፊዎቹ መነሻ የሆነ ግንዛቤን በመጨበጥ ለቀጣይ ስራዎች ለማነሳሳት መሆኑን ገልፀው ጋዜጠኞችና የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎቹ ለመነሻነት ያገኟቸውን ሀሳቦች መነሻ በማድረግ በቀጣይ የሚሰራውን ሀገራዊ ንቅናቄ በስራቸው እንዲደግፉት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ስልጠናው በዛሬው እለትም ቀጥሎ ይውላል፡፡
የካቲት 7/06/2011 ዓ.ም
ቡሾፍቱ
********************************************************************************