የአካባቢ ብክለት ችግሮችን ለመፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
ግንቦት 28/2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ
***
የ2016 ዓ.ም አካባቢ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ “የመሬት ማገገምን፣ በራሃማነትና ድርቅን ለመቋቋም” (“Land restoration, desertification and drought resilience”) በሚል ቃል ተከበረ ።
መርሐ-ግብሩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ ዣንጥራር አባይ በአካባቢ ችግሮች ምክንያት የሙቀት መጨመር፣በረሃማነት መስፋፋት፣ ድርቅ መጨመር ፣ የብዝሐ ሕይወት መመናመን ፣ የአካባቢ ብክለት፣ ፣የጎርፍ አደጋ የመጨመር እና የምግብ እጥረት ዋና ዋና የተከሰቱ የአለማችን ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል ። ምክትል ከንቲባው በገለፃቸው የአካባቢ ብክለት ችግሮች በአለማችን አስደንጋጭ ሁኔታዎችን መፍጠራቸውን በመግለፅ ይህንና በህገ መንግስታችን በአንቀጽ 44 እና 92 ስር የተደነገጉትን ድንጋጌዎች የዜጎችን በንፁህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብት እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል። በሀገራችን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ የአረንጓዴ አሻራ፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ፣የደረቅ በቆሻሻ አያያዝ ፣የኮሪደር ልማት እና " ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ " የህዝብ ንቅናቄዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን በመግለጽ ሆኖም ከፈጣን ልማት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የአካባቢ ችግሮች ከፍተኛ በመሆናቸው ችግሮቹን ለመፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል ።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው የዓለም የአካባቢ ቀን የሚከበረው ህብረተሰቡ አካባቢውን ለኑሮ የተመቸና ፅዱ ማድረግ እንዲችል ለማስገንዘብና ወደፊትም የተሻለና የተመቻቸ አካባቢን አንዲፈጥር ለማበረታታት እና የአካባቢ ልማትና ደህንነትን የተመለከቱ ጉዳዮች ሲታቀዱ በንቃት ተሳታፊ እንዲሆን ለማስቻል መሆኑን ገልፀዋል። ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ሁሉም ባለድርሻ አካላት አካባቢያቸውን ከብክለት እንዲጠብቁ ፣ የተጎዱ መሬቶችን መልሶ ማገገም ስራ እንዲሰራ በረሃማነት እና ድርቅን ለመከለከል ፣ የአረንጓዴ አሻራ ስራን በማሳካት ረገድ በቁርጠኝነት መንፈስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ ለዜጎች ምቹ የኑሮ አካባቢ ለመፍጠር እና የሀገራችንን ብልጽግናን እውን ለማድረግ እየተስተዋሉ ያሉ የአካባቢ ችግሮችን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል ።
በመርሐ-ግብሩ የእለቱን መሪ ቃል የሚያጠናክሩና በቀጣይ በሚጠበቁ ውጤቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ጽሑሮች በምሁራን ቀርበው የፓናል ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በበዓሉ ላይ ከወረቀት የተሰሩ እና አካባቢን የማይበክሉ መያዣዎች፣ የሶላር ምርቶች ኤግዚቢሽን የተካሄደ ሲሆን የፌዴራል ፣የክልሎች አከባቢ ጥበቃ ኃላፊዎች ፣ የአለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች፣የተማሪዎች ተወካዮች ፣ ከዩንቨርሲቲዎች፣የምክር ቤት አባላት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።