የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አመራሮችና ሠራተኞች በዱከም ወረዳ አድአ ቀበሌ በመገኘት በሀምሌ 22/2011 ዓ.ም "ለአረንጓዴ አሻራ" ቀን በዘርፉ የተተከሉ 6500 ያህል ችግኞችን እንክብካቤ ስራ ሰርተዋል፡፡
ሰራተኞቹ ከወር በፊት በተመሳሳይ ተገኝተው የኩትኳቶና በሞቱ ችግኞች እግር የመተካት ስራ የሠሩ ሲሆን አሁን በተደረሰበት የጊዜ ርዝማኔ የወቅቱ ተግባር የሆነውን በችግኙ ዙሪያ አካባቢ የበቀሉ ሌሎች እፅዋቶችን በማጨድና በችግኙ ዙሪያ የመጎዝጎዝ ስራና እነደየ አስፈላጊነቱ ውሀ የማጠጣት ስራ ይተከናውኗል፡፡
በችግኙ ዙሪያ የሚገኙ ባዕድ እፅዋትን አጭዶ በዙሪያው የመጎዝጎዝ ተግባር ጠቀሜታም:-
* የፀሀይ ብርሃን ከለላን በማስወገድ ችግኞች ምግብ እንዲያዘጋጁ ለማመቻቸት፣
* ባእዱ ችግኝ ከዋናው ችግኝ የሚሻማውን የምግብ ንጥረ ነገር ለመቀነስ/ማስወገድ፣
* የሚታጨደውን ሳር በችግኙ ዙሪያ በመጎዝጎዝ በትነት መልክ የሚባክነውን ፈሳሽ ለመቀነስ የሚሉት ከበርካታ ጠቀሜታዎች የተወሰኑት ናቸው፡፡
በዘመቻው ላይ የተሳተፉት የኮሚሽኑ የደን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ ከበደ ይማም ስራው ሲጠናቀቅ ለሰራተኞች ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት "ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በተከላ ወቅት በገቡት ቃል መሠረት የተከሏቸውን ችግኞች ተንከባክበው ለቁም ነገር ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው በዚህ መሠረት የኮሚሽኑ ሰራተኞች ማሳያ ሆኖ ሌሎችን እንደሚያነሳሳ እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡"
በተመሣሣይ መልኩ በዘመቻው ላይ ተሳትፈው ለጋዜጠኞችና ለሠራተኞች መልዕክት ያስተላለፉት የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንዳሉት "ባለፈው ክረምት ወቅት በሀገራችን በተከናወነው የችግኝ ተከላ ዘመቻ የተነሳ የሀገራችን ዓለማቀፋዊ ተሰሚነት በአየር ንብረት ለውጥና ተዛማጅ ድርድሮች እያደገ 2ምጣቱን ገልፀው ከዚህ አኳያ ሀገራችን የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ የገባችውን ቃል በተግባር ለመፈፀም ያላትን ቁርጠኝነትም ያሳየችበት ስራ ነው" ብለዋል፡፡
ክቡር ኮሚሽነሩ አክለውም የአካባቢና ደን ስራዎች አሁንም ሀገራዊ አጀንዳዎች ሆነው መቀጠላቸውን ገልፀው ተግባሩ ከአካባቢያዊና ስርዐተ ምዳራዊ ጠቀሜታው በተጨማሪ በሆነ ባልሆነ አሉባልታ የተጠመደውን የማህበረሰብ ክፍል ከቂምና ከጥላቻ በማላቀቅ ሀገራዊ አንድነትና አብሮነትን ለማጠናከር ያለው ፋይዳ ጎልቶ የታየ ስለሆነ መላ የሀገራችን ህዝቦች ይህንኑ በጎ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡