የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ኮሚሽን የደን ዘርፍ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለድርሻዎችና ባለሞያዎች የደኑ ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክተውን ኢኮኖሚያዊ ሚና አስመልክቶ ምክክር ተካሄደ፡፡ የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የደን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ ከበደ ይማም እንደገለፁት ሀገራችን ባላት ለብዝሀ ህይወትና እፅዋት የሚስማማ የአየር ንብረት ተስማሚነት ምክንያት በርካታ የደን ሀብት ዝርያዎች ያሉባት ሀገር ናት ብለዋል፡፡ ክቡር ኮሚሽነሩ በንግግራቸው አክለው እንደገለፁት በሀገራችን የደን ሀብት ለህዝባችን የለት ከለት ኑሮና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው መተኪያ የሌለው መሆኑን ገልፀው በተለያዩ ምክንያቶች የደን ሀብቱ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት እያበረከተ ያለው ፋይዳ ከአበርክቶው ጋር ሲነፃፀር ደካማ ነው ብለዋል፡፡
ክቡር ኮሚሽነሩ አክለው እንደገለፁት የምክክሩ ዓላማ የደን ሀብታችን በተለያዩ አግባቦች ለኢኮኖሚው እያበረከተ ያለውን ሚና በተደራጀና በእውቀት ላይ በተመሠረተ አግባብ ለሚመለከታቸው ለፓሊሲ አውጪዎችና ለሚመለከታቸው አካላት ማሣወቅ እንደሚገባ ተገልፇል፡፡ በመሆኑም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዘርፉ እያበረከተ ያለውን አዎንታዊ ድርሻ በተናበበና በተቀናጀ አግባብ መያዝና ለጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተገልፇል፡፡
በምክክር መድረኩ ከምርምር ተቋማት፣ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ፣ ከፕላን ኮሚሽንና መሠል ተቋማት የተጋበዙ የስራ ሀላፊዎችና ባለሞያዎች የተሳተፉ ሲሆን፡-
* የደኑ ዘርፍ ስርዐተ ምዳር ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እያበረከተ ስለሚገኘው አዎንታዊ ድርሻ ዳሠሳ እና፣
* ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደኑ ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ በቋሚነት እያበረከተ ያለውን ድርሻ ማጤንን የተመለከቱ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
ባለፉት አመታት ኮሚሽን መ/ቤቱ ከኤፍ.ኤ.ኦ. ጋር በመተባበር ባከናወነው የደን ሀብት ሽፋን ቆጠራ ሀብቱ ከነበረበት ወደ 15.5% ማደጉ የተረጋገጠ ሲሆን በሁለተኛው የሀገራዊ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድም ሽፋኑን ወደ 20% ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ይሁንና የደን ሀብታችንን ነባራዊና ተቀያያሪ ነባራዊ ሁኔታዎች የሚያሣይ የተቀናጀና የተደራጀ የመረጃ ስርዐት፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ማዕከል ያደረጉና ሊተገበሩ የሚችሉ ጥናትና ምርምሮችን በቀጣይነት ማካሄድና መተግበር፣ ብሄራዊ የደን ሀብትና ሀብቱ የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከማሣወቅ፣ የደን ሀብቱ የጠቀሜታ ኡደትን በአግባቡ ለይቶ ከማወቅና ከማሣወቅ ረገድ፣ የደን ሀብት ስርዐተ ጠቀሜታን ስለማሻሻል በቀጣይነት ትኩረት ተሠጥቶባቸው መሠራት እንደሚገባ ተገልፇል፡፡
የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በሁለተኛው ሀገራዊ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የደኑ ዘርፍ ለሀገራዊ ገቢ የሚያበረክተው ድርሻ ከነበረበት 4% ወደ 8% ለማሣደግ ታቅዶ ስኬት እየተመዘገበ እንደሚገኝም በውይይት መድረኩ ላይ ተገልፅዋል፡፡
የካቲት 2011 ዓ.ም ቢሾፍቱ