በከፍተኛ ቦታዎች የአየር ንብረት ለውጥን ተፅኖዎች ለማጣጣም ታስቦ በትግበራ ላይ በሚገኘው ፕሮጀክት አፈፃፀም ላይ ግምገማዊ ውይይት ተካሄደ።
መስከረም 21፣ 2013 ዓ.ም
ቡሾፍቱ-ኦዳ ነቤ ሆቴል
*********************®*******************
ኢትዮጵያ እ.አ.አ. ከ2011 ጀምሮ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስልት(CRGE) ቀርፃ ወደ ስራ በመግባት በርካታ ውጤቶችን አስመዝግባለች። ስልቱን ተግባራዊ ለማድረግ በመንግስትና በተለያዩ የልማት አካላት አካላት የተለያዩ ዕቅዶች፣ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ተቀርፀው በመተግበር ላይ ይገኛሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና ምላሹንም ለመከላከል ከሚተገበሩ አበይት ስልቶች መካከል ተፅዕኖውን የማጣጣምና የማስተሰረይ (Adaptation & Mitigation) ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ እነዚህን ስልቶች በአግባቡ በመተግበርም በአንድ በኩል የአየር ንብረት ለውጥ ተፅኖን መቀነስና የተከሰቱ ችግሮች ካሉ ደግሞ ችግሮቹን መቋቋም የሚችል (Resilient) አካባቢና ማህበረሰብ መፍጠር ነው።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ስልት በሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ዕቅዶች ተካቶ የሚተገበር ሲሆን መደበኛ የሆነውን የመንግስት ጥረት በመደገፍ የታቀዱ ግቦችን በታቀደው ልክ፣ ጥራትና ጊዜ እንዲሁም ስራዎቹ የሚፈልጉትን ሀብት በሚፈልጉት መጠን ለመደገፍ የተለያዩ ስትራተጂካዊ እርምጃዎች(Strateguc Initiatives)ተቀርፀው በሀገር አቀፍ ደረጃ በመተግበር ላይ ይገኛሉ።
የከፍተኛ ቦታዎች የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣም ፕሮጀክት የተባለው ስትራተጂካዊ እርምጃ እ.አ.አ. ከ2018 ጀምሮ በሀገራችን በሚገኙ አራት የተመረጡ ክልሎችና ስምንት ከፍታማ ወረዳዎች ውስጥ በመተግበር ላይ የሚገኝ ሲሆን የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማም በከፍታማ አካባቢዎችና በስፍራው በሚገኙ የተመረጡ ስፍራዎች የደረሠውን የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅኖ የተቀናጀ ምላሽ በመስጠት የአካባቢና ማህበራዊ ስብራቱን ማከም ነው።
ፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱ ዛሬ በቡሾፍቱ ከተማ ፕሮጀክቶቹ ከሚገኙባቸው ክልሎችና ወረዳዎች ከተወከሉ አመራሮች፣ ከፕሮጀክቶቹ ሳይቶቹ ሀላፊዎችና ከኮሚሽኑ የተለያዩ የስራ ሂደቶች ከተውጣጡ አመራሮችና ባለሞያዎች የፕሮጀክቱን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ጀምሯል።
የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ወልደየስ በውይይቱ መግቢያ እንደገለፁት "የውይይቱ ዓላማ ፕሮጀክቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተጨባጭ ስራዎች ከተግባሪዎች ሪፖርት በመነሳት መፈተሽና ጥንካሬና ድክመቶችን በአግባቡ ለይቶ ለቀጣይ ስራ ዝግጅት ማድረግ ነው" ብለዋል።
ውይይቱን በይፋዊ ንግግር የከፈቱት በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ዘርፍ ም/ኮሚሽነር በበኩላቸው እንዳሉት ". . . ይህ ውይይት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ ስራዎችና ግንኙነትን መልሶ ለማስቀጠልና ስራውን በቁልፍ ባለድርሻነት የምትመሩት አካላት ጥልቅ ውይይትና ግምገማ በማድረግ የልማት ስራው ቀጣይ ስለሚሆንበት አመቺ ሁኔታን መፍጠር ነው" ብለዋል።
ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረቡ ሪፖርቶችን አስመልክቶ የተነሱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ እርስ በርስና ከሌሎች መሠል ስራ ከሚሰሩ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራትን አስመልክት፤ የመስክ ምልከታና ልምድ ልውውጥን አስመልክቶ፤ የሪፖርቱ ፊዚካል ስራና ለስራው የወጣ ገንዘብ አሰራርን አስመልክቶ፤ የፕሮጀክቱን ስራዎች በድረ ፕሮጀክት ዘመን ለማስቀጠል እየተከናወነ ባለ ዝግጁነት አስመልክቶና መሠል ጥያቄና አስተያየቶች ቀርበው በሚመለከታቸው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
ውይይቱን በጥልቀት ለመተንተንም በቡድን በመከፋፈል እያንዳንዱን የፕሮጀክት ሳይቶች አፈፃፀም መፈተሽ የተቻለ ሲሆን በርካታ ገንቢ ግብዐቶች ተለይተው የቀጣይ እቅድ አካል እንዲሆኑ መግባባት ተፈጥሯል። ውይይቱ በነገው እለትም ቀጥሎ ይውላል።