በአጠቃላይ በአካባቢ ህጎች ምንነትና ተከባሪነት በተለይም ደግሞ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ አትኩሮ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ስልጠና የሚዲያ-ኮሙኒኬሽን ፎረም በማቋቋም ተጠናቀቀ፡፡
ዛሬ ቀጥሎ በዋለው ስልጠና ከትላንት ፅሁፎች በተጨማሪ፡-
- በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስልትና ስልቱ ለአካባቢ ብክለት መቀነስ ስለሚከተላቸው መንገዶች፣
- አዲስ ተጠንቶ ወደ ስራ ሊገባ ዝግጁ በሆነው የሰነ ምህዳር ዋጋ ትመናና ክፍያ(payment for ecosystem services) እና
- የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ፖሊሲ ላይ ገለፃዎች ቀርበዋል፡፡
በቀረቡት ፅሁፎች ላይ ውይይት የተከናወነ ሲሆን ከተሳታፊዎች አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበው የሚመለከታቸው የስራ ሀላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከተነሱ ጥያቄዎች መካከልም ኮሚሽኑ እየሰራቸው የሚገኙ ስራዎች ዘርፈ ብዙና ጥልቅ ሳይንሳዊ እውቀትን የሚጠይቁ ሆነው ሳለ ለስልጠናው የተመደበው ጊዜ አጭር ስለሆነ ሙሉ ግንዛቤ ለመጨበጥ አዳጋች መሆኑን በመግለፅ በቀጣይ እያንዳንዱ ዘርፎች በጥልቀት ስልጠና ቢሰጥባቸው ስራቸውን እንደሚደግፍላቸው ገልፀዋል፡፡
ለስራው ቀጣይነትና ጥልቀት ላለው ስራ ይረዳቸው ዘንድ ኮሚሽኑ ይህንን መድረክ የጋራ ፎረም መመስረቻ በማድረግ እንደየ አስፈላጊነቱ በየሦስት ወይም ስድስት ወራት በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ በጋራ ለመምከር ኮሚሽኑ ፍላጎት እንዳለው በማስረዳት የጋራ ፎረሙ በይፋ መቋቋሙ ተበስሯል፡፡
በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ያግዛቸው ዘንድም አካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥን የተመለከቱ ፖሊሲዎች፣ ህጎችና የስትራተጂ ሰነዶች ቅጂ የተሰራጨ ሲሆን ጋዜጠኞቹ ያላቸውን እውቀት ተጠቅመው እንዲሠሩ መግባባት ተችሏል፡፡
በመጨረሻም ጋዜጠኞቹ የጨበጡትን ግንዛቤ መነሻ በማድረግ በሀገር ደረጃ የሚቀጣጠለውን የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ንቅናቄ ስኬታማ ለማድረግ የራሳቸውን የማይተካ ድርሻ እንዲያበረክቱ ስልጠናውን የዘጉት በኮሚሽኑ የኮሚሽን ፅ/ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ካሣሁን ዋቅወያ ከአደራ ጋር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የካቲት 8/06/2011 ዓ.ም
ቡሾፍቱ
****************///******************