Friday, 27 September 2024

በዘርፍ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ደረጃ በመተግበር ላይ ያለው ለዓየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ስልት አተገባበር በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ ተገመገመ፡፡

በዘርፍ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ደረጃ በመተግበር ላይ ያለው ለዓየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ስልት አተገባበር በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ ተገመገመ፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ሉላዊ ተፅእኖ ለመቀነስና በሂደትም ለማስቆም የሚደረገውን ዓለማቀፋዊ ጥረት በቀዳሚነት የደገፈችና ተግባራዊ ስራዎችንም የሠራች ሀገር ነች፡፡ እ.አ.አ. በ2011 ደቡብ አፍሪካ ደርባን ላይ በተካሄደው የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ የእድገት መንገድ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስልትን(CRGE) የተከተለ እንደሆነም ለዐለማቀፉ ማህበረሰብ ይፋ አድርጋለች፡፡

የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር የልማት ስትራተጂ ዘላቂ ልማትን ሊያመጣ በሚችል ሁኔታ የተቀረፀና ከመደበኛ ሀገራዊ የልማት ስልቶች ጋር ተጣጥሞ የሚተገበር ነው፡፡ ትግበራውም ልማትን በሚያከናውኑ ዘርፍ መስሪያ ቤቶች በሙሉ ተካቶ የሚከናወን የአረንጓዴ ልማት ስልትን((Green Growth)የሚከተል ሲሆን መስሪያ ቤቶቹ የሚያከናውኗቸውን የልማት ስራዎች በአረንጓዴ የልማትና የእድገት መስመር እንዲተገብሩ የሚያደርግ ነው፡፡

የአረንጓዴ ልማት ስልት በሁሉም የመንግስትና የግል አልሚም መተግበሩ ታሣቢ የተደረገ ሲሆን በተለይም ለስትራተጂው ስኬት ቁልፍ ሚና አላቸው ተብሎ የተለዩ ዘርፎች አምስት ሲሆኑ እነሱም፡-

  • ግብርና፣ ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንስሳት ሀብት ልማት
  • ደን ልማትና ጥበቃ (አካባቢና ደን)፤
  • ንግድና ኢንዱስትሪ፤
  • ትራንስፓርት፤
  • ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን እና
  • ውሀ፣ መስኖና ኢነርጂ ናቸው፡፡

እነዚህ ተቋማት በሚያከናውኗቸው የልማት ተግባራት የአረንጓዴ ልማት ስልትን የተከተለ መሆኑ እንዲረጋገጥ የሀብትና የቴክኒክ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን ስራውንም በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲያስተባብር ለአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ተሰጥቶታል፡፡

ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት መደበኛው የመንግስት አሠራርና አመራር እንደተጠበቀ ሆኖ በሁሉም ስልቱ የተማከለባቸው መ/ቤቶች ውስጥ ራሱን የቻለ የስልቱ አስተግባሪ ዲፓርትመንት እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡ ስራውን በቅንጅት ለመምራትና ለመደገፍ ይቻል ዘንድም ከየመስሪያ ቤቶቹ የተውጣጣ የቴክኒክ ቡድን የተደራጀ ሲሆን የስራቸው አፈፃፀምም በየሶስት ወሩ እየተገመገመ እንደየአስፈላጊነቱ ሚኒስትሮቹ አባል ለሆኑበት ብሄራዊ ኮሚቴ እየቀረበና የጋራ አቅጣጫ እየተሠጠበት ይተገበራል፡፡

በዚሁ መሠረት ከየካቲት 1-2/2011 ዓ.ም የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ አጋማሽ ለመገምገም የቴክኒክ ኮሚቴው በአዳማ የባ ሆቴል ግምገማ አድርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ በኮሚሽን መ/ቤቱ የሲ.አር.ጂ. ፋሲሊቲ ማስተባበሪያ የተጠናው ሀገር አቀፍ የዳሠሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ ስትራተጂውን በተሻለ ሁኔታ ለመተግበርና በተለይም የሙቀት አማቂ ጋሶች ልቀት ቅነሳ ልኬትን ለመተግበር የሚረዳ ብሄራዊ ፍኖተ ካርታ(Road Map)ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

በቀጣይነት የሴክተር መ/ቤቶች የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ተገምግሟል፡፡ በግምገማው በርካታ ጠንካራ ስራዎች በስትራተጂው መሠረት እየተከናወኑ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን አሁንም ለዘርፎች የተሰጡ ተግባራት ላይ አትኩሮ ከማቀድና ከመፈፀም፣ ወጥ አደረጃጀት ከመዘርጋት፣ ወቅትን ጠብቆ ሪፖርት ከማቅረብ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸው ተነስቶ በመወያየት ቀጣይ የአፈፃፀም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የካቲት 2011 ዓ.ም

አ ዳ ማ

******************///*****************

የባለስልጣንኑ አድራሻ

አድራሻ፡ አራት ኪሎ ከአብርሆት ቤተመጻሕፍት በስተጀራባ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አጠገብ፣ አራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 9

ስልክ፡ +251 (0)11-170-4038/4150

ፋክስ፡ +251 (0)11-170-4158/ 45

ኢመይል   Info@epa.gov.et

ቲውተር  https://twitter.com/epaethiopia

ፌስቡክ   https://www.facebook.com/MefEth/

ቴሌግራም   https://t.me/efcccethiopia

..      12760

አዲስ አበባ, ኢትዮጵያ