ነሀሴ 5/2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኮልፌ ቀራንዮ
**********************©********************
እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም በሀገረ ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የአለም ሀገራት መንግስታት ስምምነት የደረሱበትና እንደየ ሀገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን ለመውሰድ መስማማታቸው ይታወሳል።
የስምምነቱ መሰረታዊ ቁም ነገር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተከትሎ እየተከሰቱ የሚገኙ ሁኔታዎችን ለመግታት ሀገራቱ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የሙቀት አማቂ ጋሶች ልቀትን በመቀነስ (Green house gases emmission reduction) እና የማጣጣሚያ ተግባትን በማከናወን የአየር ንብረት ለውጡ የሚያስከትላቸውን መዘዞች መግታት ነው።
የዘርፉ ባለሞያዎች እንደሚተነትኑት የኢንዱስትሪ አብዮት በተቀጣጠለበት በ19ኛው ክ.ዘመን የከባቢ አየር የሙቀት መጠን ከ1°ሰልሺየስ በታች የነበረና ለሰው ልጆችና ለአካባቢ ምቹ የነበረ ሲሆን ከዚያ ወዲህ ለመልማትሲባል በሰው ልጆችና በተፈጥሮ በደረሱ ጉዳቶች ማለትም የሙቀት አxማቂ ጋዞች (GHG) ልቀት በመጨመሩ የከባቢ አየር ሙቀት ጨምሯል። በዚህም ሳቢያ ተገማች ያልሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ መከሰትን እያስከተለ ይገኛል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት አሁን ባለንበት ዘመን የከባቢ አየር ሙቀት መጠን ለሰውና ለአካባቢ አዳጋች በሆነ ደረጃ አምዕራባውያኑ የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ከነበረው ወደ 3°c ጭማሪ የሚያሳይ ሲሆን ይህንን ሁኔታ በጋራ ርብርብ በፍጥነት በቁጥጥር ስር በማዋል ዐለማችንን ከጥፋት መታደግ ይገባል። ለዚህም የአለም ሀገራት ተናጠላዊና የጋራ ርብርብ ዕቅድ ተይዞለት በመከናወን ላይ ይገኛል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ከመደረሱ ቀደም ብላ እ.አ.አ. በ2011 "ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስልትን" ነድፋ በ17ኛው የተ.መ. የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ ላለፉት አስር አመታት ስትተገብር ቆይታለች።
ይህንኑ ጥረት የሚደግፍና የስምምነቱ የሀገራት ተሳትፎን የሚያረጋግጥና "በፈቃደኛነት ላይ የተመሠረተ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቀነሻ ዕቅድ-Nationally Determined Contribution (NDC)" የተሰኘ ዕቅድ እ.አ.አ. በ2015 በማውጣት ለተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ስምምነት አስተግባሪ አካል (UNFCCC) በማቅረብ ይህንኑ ዕቅድ በመተግበር ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በነደፈችው በዚህ ዕቅድ እ.አ.አ. በ2011 ዒላማው ሲቀመጥ ወደ ከባቢ አየር ይለቀቅ ከነበረው 140 ሚሜ ቶን የካርበን ዳይኦክሳየድ እኩሌታ መጠን በተለመደው ሁኔታ ቢኬድ እ.አ.አ. በ2030 400 ሚሜ ቶን ይደርስ የነበረውን ልቀት በ250 ሚሜ ቶን በመቀነስ የሀገራችን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት የተጣራ ልቀትን (net emission) ዜሮ ፐርሰንት የማድረግ የተለጠጠ ትልም ነው።
ለዚሁ የተለጠጠ ግብ መሳካት የግቡ ዒላማ ወደ 80% ያህሉ በደንና በግብርና ዘርፎች በሚሰራው ስራ የሚሳካ ነው። በዚሁ መሠረት የደን ልማትና ጥበቃ ስራችን የዚሁ አጠቃላይ ማዕቀፋዊና ስትራተጂካዊ አላማ ማሳኪያ ሲሆን ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ስታከናውን የቆየችውን የደን ልማትን በማጠናከር እ.አ.አ. በ2030 ዓ.ም በ2015 ከነበረበት የ15% የሀገራችን የደን ሽፋን ወደ 30% ማድረስ ነው።
ለዚህም ስኬታማነት ባለፈው ዓመት የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ (Green Legacy) ችግኝ ተከላ በያመቱ በአምስት ቢሊዮን በመደመር እ.አ.አ. በ2023 ወደ 20 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከልና የፅድቀት መጠናቸውንም ከ80% በላይ በማሳካት የታለመውን አለማቀፍና ሀገራዊ ዒላማ ማሳካት ነው።
ለዚሁ አላማ መሳካት ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ 2700 ያህል ሀገር በቀል ችግኞችን ከኮሚሽናችን ጋር በመሆን የተመድ አካል የሆኑ ከሀያ በላይ ተቋማት (UN Agencies) ተሳትፈውበት ተክለዋል።
በሁነቱ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ዶ/ር ካትሪን ሶዚ እንዳሉት "ኢትዮጵያ በምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ማዕቀፍ ውስጥ እየተከናወነ ባለው የችግኝ ተከላ በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ከሚመጣ መቅሰፍት ዓለምን ለመታደግ የሚረዳ አርዐያነት ያለው ተግባር እያከናወነች ነው" ብለዋል።
የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር ፕ/ር ፍቃዱ በየነ በሁነቱ ላይ ተገኝተው ተከላውን ያስጀመሩ ሲሆን ባደረጉት የማስጀመሪያ ንግግር "የተመድ የኢትዮጵያ ተወካዮች የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ጥረት በተግባር በመደገፋቸው ምስጋና በማቅረብ ይህንን የሀገሪቱን ጥረት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ ረገድ የበኩላቸውን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።"