የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ኢንጂ. ለሊሴ ነሜ ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ፕሮግራም (UNEP) የኢትዮጵያ ተወካይ ከሆኑት ክብርት ማርጋሬት ኦዱክ ጋር የስራ ትውውቅ አደረጉ፡፡
ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች የአካበቢ ጥበቃ ጉዳይ ላይ ሀገራችን ከባለብዙ ዘርፍ ስምምነቶች (Multilateral Environmental Agreements) ወደ ተግባር ለማስገባትና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ያላትን ግንባር ቀደምት ሚናን በላቀ ደረጃ የምታራምድበትና ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮችን በመቀመር ለማስፋፋት የሚያስችሉ ተግባራትን በቅንጅት ለመተግበር በቀጣይ እንደሚሰሩ ተወያይተዋል፡፡
ክብርት ኢንጂ. ለሊሴ ሀገራችን አካባቢን ለመጠበቅ በልማትና በኢንቨስትመት ዕቅዶችና ፕሮግራሞች ውስጥ አካታ ለመተግበር ጥረት እያደረገችና ይህንንም በቀጣይ አጠናክራ ተምሳሌታዊ ሀገር ለመሆን በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተጀመሩ ንፁህ፣ ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን በመፍጠር ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ላይ አጋር አካላት በተለይም እንደ የዓለም አቀፍ የአካባቢ ፕሮግራም (UNEP) ድርጅቶች በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በሀብት ሊደግፉ እንዲሚገባ አንስተዋል፡፡
ክብርት ማርጋሬት በበኩላቸው ድርጅታቸው ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በአካባቢ ጉዳዮች ላይ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን እና የበኩላቸውን የአመራርነት ሚና ሁሉ ለማበርከት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ከዚህ ቀደም የተጀመሩ የጋራ ስራዎች ተጠናክረው እንዲተገበሩ እና ተጨማሪ አዳዲስ የጋራ እና የትብብር አጀንዳዎች በመቅረጽ ወደ ስራ እንዲገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡ ይህንንም ለመተግበር የባለሙያዎች ቡድን በጋራ ሰነዶችን አዘጋጅቶ ለቀጣይ የከፍተኛ አመራሮች እንዲያቀርብ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡