የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ዘርፍ ከክልልና ተጠሪ ተቋማት ሀላፊዎች ጋር የዘርፉን ስራዎች ለመገምገምና በቀጣይ ስራዎች ላይ አመራር ለመስጠት ያለመ "የኦን ላይን" ስብሰባ ተካሄደ።
በአካባቢ፣ በደንና በአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከክልልና ተጠሪ ተቋማት ሀላፊዎች ጋር የዘርፉን መደበኛ ስራዎች ነባራዊ ሁኔታ ለመገምገምና በቀጣይ የትኩረት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ "የኦን ላይን" ስብሰባ ተካሄደ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር የተከበሩ ፕ/ር ፍቃዱ በየነ ከዘርፉ አመራሮች ጋር በኢንተርኔት ባደረጉት ውይይት ለተሳታፊዎች እንደገለፁት የውይይቱ ዓላማ "በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የዘርፉ ስራዎች ከተቀመጠው ተልዕኮ እንዳይስተጓጎሉ የተለያዩ የስራ መርጃ ቴክኖሎጂዎችን በተለይም የመረጃ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በታቀደው ልክ ስራዎችን ማሳካት እንደሚገባና በነባራዊና ቀጣይ ስራዎች ላይም አመራር ለመስጠት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ለሀላፊዎቹ ባደረጉት ገለፃ በተለያዩ ተቋማዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይም ትኩረት ያደረጉት:-
* የዘርፉ መደበኛ ስራዎች ሳይስተጓጎሉ ማሳካት ስለሚቻልባቸው መንገዶችና ከስራዎች አፈፃፀም ግምገማ፣ ክትትልና ድጋፍ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች፤
* ኮቪድ-19 በዘርፉ ስራዎች ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ
ተፅኖ ለማካካስ ይቻል ዘንድ የ"ኮቪድ ሪስፖንስ ፕላን"
በኮሚሽን ደረጃ መዘጋጀቱንና የክልልና ተጠሪ ተቋማት ዕቅዱን
ወስደውና ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ወደ
ተግባር እንዲገባ በሚያስችሉ ጉዳዮች፣
* በግንቦት 28/2012 " አካባቢ ጥበቃ ለዘላቂ የብዝሀ
ህይወት ልማት" በሚል መሪ ቃል በሚከበረው የዓለም አካባቢ
ቀን አከባበር ዕቅድና ክልሎች ሊከተሉ በሚገባቸው የአሰራር
አቅጣጫዎች ላይ፣
* በዘንድሮው "የአረንጓዴ አሻራ" ሀገራዊ የችግኝ ተከላ ላይ
እየተከናወኑ ባሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ነባራዊ
እውነታዎችና ስራውን ከዘርፎች ጋር በመቀናጀት እንዴት
በግንባር ቀደምነት መምራት እንደሚገባና፤
* የአብዛኛው ስራዎች ስትራተጂካዊ ድጋፍ በሆነው
የማህበረሰብ ንቃት ማጎልበትና የህዝብ ንቅናቄ አስፈላጊነትና
መከተል በሚገባን ስልቶች ላይ አብራርተዋል፡፡
በተደረገው ሰፊ ገለፃ ላይ በመመርኮዝ የተወሰኑት ሀላፊዎቹ በራሳቸው እያከናወኑ ባሏቸው ስራዎች ላይ ማብራሪያዎችን ያቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎቹ በተነሱ ጥያቄዎችና ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ላይ አመራር በመስጠት በቀጣይ በዚሁ ፕላት ፎርም በመጠቀም ግንኙነቱ እንደሚቀጥል ተገልፆ የእለቱ ምክክር ተጠናቋል፡፡