በኤፌዲሪ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ ኃይል ባለስልጣን ሲ.ቲ.ኦ.ኤን/ዩኒዶ (CTON/UNIDO)ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር የኤሌክትሪክ ኃይልን የሚቆጥቡ የምግብ ማብስያ ደረጃ ለማወጣት የሚያስችል ጅምር ምክክር ከባለድረሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ራማንዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተካሄደ፡፡
አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት ወ/ሮ የአምላክሥራ ታመነ እንደተናገሩት "ታዳሽነታቸው የተረጋገጡ የቴክኖሎጂ ልማት ውጤቶችን ለኃይል አቅርቦት አገልግሎት ማዋልና ሀገራችን ለቀየሰችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መሣካት ወሳኝ ነው" ብለዋል፡፡
በኮሚሽኑ የቴክኖሎጂ ስርፀትና ማስፋፋት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ የአምላክ ስራ በመክፈቻ ንግግራቸው አክለው እንደገለፁት "ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ለፍጆታችን ከመጠቀም ጎን ለጎን በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ ምድጀዎች በኃይል ምንጭነት መጠቀም የደን ጭፍጨፋን የሚቀንስና የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነትን የሚያስቀር ነው" ብለዋል፡፡
ሀገራችን የምታመርተውን የኤሌክትሪክ ኃይል በቁጠባ ለመጠቀም ያስላችላት ዘንድ የኃይል አማራጮችን ማበራከትና ያሉትን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል የአጠቃቀም ደረጃዎች መውጣት ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነና የሀይል አጠቃቀማችን ደረጃ ካልተበጀለት በውድ ዋጋ የሚመረተውን የኤልክትሪክ ኃይል ለከፍተኛ ብክነት ስለሚዳረግ ሀይል አቅራቢ የሆነውን መንግስትና ተጠቀሚውን ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋል፡፡
የኤሌክተሪክ ኃይል ብክነት አላስፈላጊ ወጪን ከመዳረጉ በተጨማሪ ለአካባቢ ሙቀት መጨመር ድርሻ ስላለው የደረጃ ማውጣቱ ተግባር በአፋጣኝ ተሠርቶ ወደ ትግበራ መግባቱ ጊዜ ሊሠጠው የማይገባ ጉዳይ መሆኑ በምክክሩ ላይ ተነስቷል፡፡ በመሆኑም ሥራውን ለማስጀመር የባለድረሻ አካላት ተሳትፎና አጋርነት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተገልፅዋል፡፡
በውይይት መድረኩ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የኃይል መፈተሻ አሰራር ዘዴዎችና ምርጥ ምድጃዎችን ማህበረሰቡ በምርጫ እንዲጠቀም የሚያስችሉ የኮሙኒኬሽን ስራዎች የተመለከቱ ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተሰጠ ሲሆን ተገቢው ምላሽም ተሠጥቶበታል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታም የኤልክትሪክ ማብሰያ ምድጃዎች የኃይል አጠቃቀም ደረጃዎች ማውጣት ስራ እንደተጀመረ ከመደረኩ ተገልፅዋል፡፡
የካቲት 2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ
**********@@@*********
በ፡ አበጀ ታሪኩ