የጣሊያን መንግስት ለአካባቢ ጥበቃና ልማት ትብብር የሚውል የአስራ አንድ ሚሊዮን ዩሮ ለሶስት የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት ማፅደቁ በአዲስ አበባ ራዲሰን ብሉ ሆቴል በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ ተገለፀ፡፡ የምክክር መድረኩ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከዓለማቀፉ የአረንጓዴ ልማት ተቋም (Global Green Growth Institute-GGGI)ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡ ዓላማውም በሀገራችን የሚገኙ የግል የቢዝነስ ተቋማት፣ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በተለያዩ አካባቢያዊ ጉዳዮች ማለትም በታዳሽ የሀይል ምንጭ፤ በውሀ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም፣ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች አያያዝና አወጋገድ፣ በአካባቢ ቴክኖሎጂዎች አያያዝና አጠቃቀም እና መሰል ከአካባቢ ልማትና ጥበቃ ዙሪያ ሀገራቱ በፓሪስ ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ የሚያከናውኑዋቸውን የልማት ስራዎች በጣሊያን መንግስት የሚደገፉባቸውን ሁኔታዎች ለማመቻቸትና በጋራ ስለሚሰሩባቸው ሁኔታዎች ለመለየት ነው፡፡
የአውደ ጥናት መድረኩን የከፈቱት በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የሀብት ማፈላለግና የፕሮጀክቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ወርዲ ሃሽም መንግስታችን በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሠውን ተጽዕኖ ለመከላከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን በመንደፍ የአረንጓዴ ልማትና እድገት አማራጭ ሲተገብር ቆይቷል ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በልማት አማራጫችን ተከታታይና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ከማምጣት ጎን ለጎን በአረንጓዴ የልማትና እድገት መስመሩ በሂደት አማካይ የከርበን ልቀት ዜሮ በማድረስ (zero carbon net emission) በ2017 ዓ.ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በትግበራ ላይ መገባቱን አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም አሉ ኮሚሽነሩ ስትራተጂያችንን በአግባቡ በመተግበር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጣውን ተጽዕኖ ለመቀነስ በመንግስት አካል ብቻ የሚሰራ ስራ ባለመሆኑ የግል ዘርፉ ከጣሊያን በዘርፉ ላይ ከተሰማሩ የግል ድርጅቶች ጋር በመቀራረብ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ በቅንጅትና በቀጣይነት በመሠራት በዘርፉ ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት በአለማቀፍ አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የአፍሪካና አውሮፓ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዲኤክስ አጎደስ እንዳሉት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአካባቢ ላይ የሚመጣውን ተጽዕኖ ለመቀነስ የግል ዘርፉ ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጣውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመንደፍ በትግበራ ላይ መሆኑ የመንግስትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የድርጅታቸው ድጋፍ በቀጣይነት እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በጣሊያን የአካባቢ፣ የመሬትና የባሕር ሚኒስቴር የዘላቂ ልማት፣ የአካባቢ ጉዳት ፣የአውሮፓ ህብረትና የአለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስ ብሩና ኮን በምክክር መድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት "በአሁኑ ጊዜ የአየር ንብረት ተጽዕኖ እየጨመረ በመምጣቱ ተጽዕኖውን ለመቀነስ የጣሊያን መንግስት ለአካባቢ ጥበቃና ልማት ትብብር የሚውልና 11 ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የሚውል የአስራ አንድ ሚሊዮን ዩሮ ለሶስት የምስራቅ ሀገራት/ለኢትዮጵያ"ለሱዳንና ለጂቡቲ/ ማፅደቁን ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ በ5 ፕሮጀክቶች ላይ የሚውል የ8 ሚሊዮን ዩሮ ድርሻ እንዳላት ሚስ ብሩና ገልፀዋል፡፡
ለኢትዮጵያ የፀደቁት አምስቱ ፕሮጀክቶች በታዳሽ የሐይል ምንጭ፣ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝ፣ የዘላቂ የውሃ አያየዝና አጠቃቀም፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተጣጣመ ግብርና(Climate Smart Agricalture) እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግስታት መካከል በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጣውን ተጽዕኖ ለመቀነስ በትብብር ለመስራት እ.አ.አ 2016 የቴክኒክ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታዋቅ ነው፡፡
የካቲት 2011 ዓ.ም
አዲስ አባባ-ራዲሰን ብሉ